ለሱማሌ ክልል ውሃ ባለሙያዎች የሚሰጠው ሥልጠና ተጀመረ

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከሱማሌ ክልል ሁሉም ወረዳዎች ለተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጠውን ሥልጠና ጀመረ፡፡ ሥልጠናው በክልሉ በሚገኙ ባለሙያዎች ላይ ያለውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ታልሞ የሚሰጥ  ሲሆን በፍላጎት ዳሰሳ ጥናትና የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታመነ ኃይሉ እንደተናገሩት ክልሉ እምቅ ሀብትና የሰው ኃይል የያዘ ቢሆንም በውሃው ዘርፍ የሚጠበቀውን ያክል አልተሰራበትም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ኢንስቲትዩቱ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡ ሥልጠናው የሚሰጠው ክልሉ በዘርፉ ያለውን አቅም አሟጦ እንዲጠቀም ታስቦ ሲሆን በተለይም የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ ፕሮጀክት አስተዳደር፣ የፀሐይ ኃይል አጠቃቀም እና ሌሎች ወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሰልጣኞቹ በሚቆዩባቸው ቀናት መሰረታዊ ክህሎት ይጨብጣሉ ብለው እንደሚያምኑም ዶ/ር ታመነ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ውሃ ቢሮ ተወካይ አቶ አብዲ ካሚል በመክፈቻው ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ተግባራዊ ሥልጠና በመስጠትና ባለሙያዎችን በማብቃት የሚታወቅ በመሆኑ በዚህ ረገድ ባለሙያዎቻችንን ያበቃልናል የሚል ሙሉ እምነት አለን ብለዋል አቶ አብዲ፡፡ በተግባር የሚሰጠው ሥልጠና ሰልጣኞቹ ወደየወረዳቸው ሲመለሱ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል፡፡

(EWTI-PRCD-6-3-14 E.C)