የሥልጠና ማጠናቀቂያ የምስክር ወረቀት ተሰጠ

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ላይ ለመከለከያ ሠራዊት አባላት የሰጠውን ሥልጠና አጠናቀቀ፡፡ ሥልጠናውን በብቃት ላጠናቀቁ የሠራዊቱ አባለትም የምስክር ወረቀት ተሰጥቷዋል፡፡ የምስክር ወረቀት አሰጣጡ ላይ የተገኙት የኢንሰቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታመነ ኃይሉ  የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት ምህንድስና ክፍል ከኢንስቲትዩታችን ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ሥልጠናም የዚህ ትብብር አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በምህንድስናው ዘርፍ ጥሩ ልምድ ያካበቱ እነዚህ አባላት በዚህ ሥልጠና ታግዘው ለሠራዊቱና ለህብረተሰቡ ለሚሰጡት አገልግሎት የድርሻችንን በማበርከታችን ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡ በተለይም በዚህ ወቅት ለመከላከያ ሠራዊታችን ይህንን ሥልጠና በመስጠታችንም ዕድለኞች ነን ብለዋል፡፡

የሰልጣኞቹ ተወካይ ሻለቃ ኢብሳ ጉሳ በበኩላቸው የሠራዊቱንና የህብረተሰቡን የውሃ ችግር ለመፍታት ይህ ሥልጠና በጣም ወሳኝ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ሥልጠናው የተግባር መሆኑ ትክክለኛውን ክህሎት አስጨበጦናል በማለተ የሥልጠናውን ጠቀሜታ ገልጸዋል፡፡ አክለው ያገኘነው ሥልጠና የላቀ አገልግሎት እንድንሰጥ ይጠቅመናል ያሉት ሻለቃ ኢብሳ ይህን ዕድል ላመቻቸላቸው የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምስጋናቸውን አቅረበዋል፡፡

በመጨረሻም የመከላከያ ሚኒስትር አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መሐሪ እና የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶር ታመነ ኃይሉ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡  

(EWTI-PRCD-30-2-2014 E.C)