የፀረ-ሙስና ቀን ተከበረ

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንሰቲትዩት አመራርና ሰራተኞች በዓለም ለ17ኛ በሀገራች ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ-ሙስና ቀን በውይይት አከበሩ፡፡ ወይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታመነ ኃይሉ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት በሀገራችን በሁሉም አቅጣጫ እየታየ ያለው የሥነ ምግባር ዝቅጠት ከዚህ በፊት ትውልዱን በሥነ-ምግባር ለማነፅ ያልተሰሩ ስራዎች ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የመንግሥትም ሆኑ የግል ተቋማት ሠራተኞቻቸውን በመልካም ሥነምግባር የመገንባት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እቅዳቸውን ለማሳካት የተመደበላቸውን በጀትና ንብረት በአግባቡ ለመጠቀም በመልካም ሥነ-ምግባር የተገነባ ሠራተኛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ እኛም የሥነምግባር ጉዳይን አጀንዳችን አድርገን ከየእለት ተግባራችን ጋር ልናስተሳስር ይገባል፡፡ እሴቶቻችን ናቸው ብለን ያወጣናቸውን ቁምነገሮችም ከጽሁፍ አልፈን በዕለት ተዕለት የሥራ ውሎአችን ላይ መንጸባረቅ አለባቸው፡፡ መልካም ሥነምግባር በቅጥር፣ በሠራተኛ ምልመላ፣ በእድገትና ዝውውር ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል፡፡ በተጨማሪም በየደረጃው የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችንና ሌብነትን አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ከሙስና ነጻ ስለማያደርገን እንደግለሰብ ራሳችንን ነጻ ከማድረግ በተጨማሪ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ታግለን ማሻሻል ይጠበቅብናል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት የፌዴራል ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለሙያ እንደገለጹት ሙስና አደራ መብላትን፣ የህዝብ ሥልጣንን ለግል መጠቀም፣ ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል መርህ መጣስ፣ ፍትህን ማዛበት ነው ብለዋል፡፡ ሙስና በጥንቃቄ የሚፈጸም በመሆኑ አሻራው በቀላሉ ስለማይለይ መሰረት ባለው የሥነ-ምግባር ትምህርትና በሰዎች አሰተሳሰብ መለወጥ የሚወገድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሙስና 5 በመቶ የዓለምን የተቆጣጠረ መሆኑንና ከዚህም ውስጥ ታዳጊ ሀገራት ሰፊውን ድርሻ እንደያዙ ለዚህም በምሳሌነት አፍሪካ ብቻ 148 ቢሊዮን ዳላር እንደምታጣ ተናግረዋል፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ ሙስና ሲንሰራፋ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ አመኔታ ማጣት፣ የተፈጥሮ ሚዛን መዛባትና ሌሎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ይከሰታሉ፡፡

ሀገራችን ኢተዮጵያ የዓለም ፀረ-ሙስና ኮነቬንሽን የፈረመች ሲሆን የተለያዩ ሀረጎችንና ደንቦችን አውጥታ እየተነቀሳቀሰች ተገኛለች፤ ይሁን እንጂ አስፈላጊው ውጤት በዚህ ረገድ እንዳልተመዘገበ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ም/ዋ/ዳይሬክተር አቶ አጃናው ፈንታ እንደተናገሩት ሁሉም ሰው ባለበት ቦታ ኃላፊነቱን ከተወጣ ምስናን የመከላከል ሥራችን ውጤታማ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት

(PRCD 01-04-2013)